Pages

Tuesday, July 9, 2013

VOICE OF OROMIA: ጉዱ የማን ሆነና?ድረስ ለአቤ ቶክቻውህን ደብዳቤ በቅርቡ “ጉድ በል ...

ጉዱ የማን ሆነና?

ይድረስ ለአቤ ቶክቻው
ይህን ደብዳቤ በቅርቡ “ጉድ በል ሰላሌ” በሚል ርእስ ባወጣኸው ላይ ተመርኩዤ የፃፍኩት ሲሆን እሱን በአንድ ቁምነገር በመያዜ ምክንያት ሳላወጣው ብቆይ ሌላ ታሪካዊ የሆነ ጦርነት በኦሮሞና በተለይም በጓደኛዬ ጃዋር ላይ ስትከፍቱ (አንድ ታዛቢ “ጨርቅ ጥሎ ማበድ” ብሎታል)በግርምት እየተከታተልኩ ቆየሁ::
ለነገሩ ለእንቶ ፈንቶ መልስ እየሰጡ እሰጥ አገባ መግጠምና ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ ባይሆንም እንቶ ፈንቶ ሲበዛ እውነት የሚመስላቸው ስለማይጠፉ መልስ መስጠት የግድ ይላል::
አንዳንድ ነጥቦችን ላንሳና ወደ ዋናው መልዕክት እሄዳለሁ::
1) ከሰሞኑ በግብፅ UNHCR ፊት ለፊት ሲካሄድ  የነበረው አሁንም እንደ ቀጠለ ነው፤ ይሁንና ከኦሮሞ፣ከግብፅና ከአልጀዚራ ድረ-ገፆች ውጭ ሲዘገብ አይታይም:: እርግጥ አንተና መሰሎችህ እንደ ዜና ሳይሆን  ሰላማዊ ሰልፈኞቹን ለማጥቃት አንድ ሰሞን አንስታችሁታል:: እሱን ወደ ኋላ እመለስበታለሁ::
2) አንተም ሆንክ መሰል ዘላፊዎች ትኩረታችሁን ያደረጋችሁት በመጀመሪያ ቀን ካነገቧቸው ወደ አስር የሚጠጉ መፈክሮች ውስጥ “ኦሮሞዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም” የሚለው ላይ ነው:: ስለአንኳር ጥያቄያቸው ሲጀመርም ደንታም የላችሁ፤ ከዚያ በኋላ የት እንደደረሱ የማወቅ ፍላጎትም የላችሁ:: አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችማ ስደተኞቹ ተሰብስበው እስር ቤት ቢታጎሩ ደስ ይላቸዋል::
3) ይሄ “ኢትዮጵያዊነትን አለመቀበል” አስተሳሰብ በ”ኢትዮጵያ አንድነት አማኞች” ዘንድ እጅግ የሚብጠለጠል ቢሆንም አሁን የመጣ ወይንም አዲስ ክስተት አይደለም:: ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ የኦጋዴን ተወላጆች፣የሲዳማ ብሄርተኞችና  ሌሎችም ይሄን አስተሳሰብና እምነት ያራምዳሉ፤ ይህም የራሱ የሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች አሉት:: ሰሞኑን ጨርቅ ያስጣላችሁ ዕብደት አደባባይ ሲወጣማ መሃል ሲያንዣብብ የነበረው ሳይቀር (“ንፁህ ኢትዮጵያውን”ን አይጨምርም) ሁሉም በየፊናው “ይሄስ ኢትዮጵያዊነት በአፍንጫዬ ይውጣ – መጀመሪያ (ብሄሩን እየጠቀሰ) ሲዳማ ነኝ ወዘተ” ማለቱን ቀጥሏል::
4)በአንፃሩደግሞ እነዚህን ወገኖች “ኢትዮጵያውያን አይደሉም” የሚሉ “ንፁህ ኢትዮጵያውን”ም አሉ:: ይሄንን አይነት “ኢትዮጵያዊነት” ደግሞ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ በጥብቅ የሚጠየፉት እንደሆነ በአንድ ወቅት ቃለምልልስ ላይ ተናግረዋል:: የኢትዮጵያው መሪ የሚዘልፉትን ዓይነት “ኢትዮጵያዊነት” የኢትዮጵያ መንግስት ግፍ ሰለባ የሆኑት አንቀበልም ቢሉ ምኑ ላይ ነው ድንቁ?
4) እሩቅ ሳንሄድ በ2012 መባቻ ላይ ቀጣሪ ጌቶችህ የ”ዓመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ” ብለው አበበ ገላውን ሲሸልሙ በዚያው ዓመት እነ ጥሩነሽ ዲባባ በኦሎምፒክ ዓለምን ሲያስደምሙ ነበር:: ታዲያ እነዚህን  ኦሮሞች እንደ “ኢትዮጵያዊ” ሳትቆጥሩ ኦሮሞው “ኢትዮጵያዊ”ነቱን ከጥያቄ ሲያስገባ “እኛ የምንተገብረውን ተረድተው ነው” አትሉም ነበር? ነው ወይንስ አበበ ገላው የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር  መለስ ዜናዊን ተሳድቦ የ”ዓመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ”ን “ክብር” ስለተጎናፀፈ አንተም ኦሮሞችን ተሳድበህ ልትሸለምበት አቅደህ ነው? እቅድህ ባልከፋ ነበር፤ ነገር ግን ኦሮሞነትህን እንደደበቅከው ብትቆይ ያዋጣህ ነበርና ተስፋ ያለህ አይመስለኝም:: በነገራችን ላይ መለስ ዜናዊን አምርሬ ብቃወምም አበበ ገላው እና አንተ እድሜ ልካችሁን የማትሰሩትን አምባገነኑ ሰው ባንድ ወር እንደሚሰሩ ጥርጥር የለኝም:: ሌላው ቢቀር ይሄን ጣጠኛ ግድብ ያስጀመሩት ሰውዬው ናቸው::
5)የኦሮሞን ጥያቄ ለማጥላላትና ለማሳነስ ልክ አንተ እንዳልከው “የተጨቆኑት ኦሮሞዎች ብቻ ናቸው እንዴ” የምትለዋ በጣም የተለመደች ናት:: ይሄ እውነት ነው፤ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ብሄሮች ለዘመናት በአምባገኖችና በጨቋኝ ተስፋፊዎች ሲበዘበዙ፣ሲዋረዱና በባርነት ሲሸጡ እንደነደነበር ዛሬም እንዳሉ የታወቀ ነው:: የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ይሄንን ይገነዘባሉ፤ መቸም እኛ ብቻ ነን ተበዳይ ብለው አያውቁም:: ጥያቄው ማተኮር ያለበት ግን ኦሮሞ ላይ የሚደርሰው ግፍ እንዴትና ለምን ተለየ የሚለው ላይ ነው:: ለዚህ ደግሞ ምስክርነት የሰጡት በኦሮሞ ህዝብ ወዳጅነታቸው የማይታወቁት ስዬ አብርሃና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው:: ሁለቱም በእስር ቤት በነበሩበት ወቅት ያስተዋሉትን ሲገልፁ እስር ቤቱ ውስጥ ኦሮሞ ከመብዛቱ የተነሳ “የእስር ቤቱ ቋንቋ ኦሮምኛ/አፋን ኦሮሞ ነው” ብለዋል:: አንዳንድ ጥናታዊ ግምቶች የኦሮሞ ፖለቲካ እስረኛ እስከ 95% ይደርሳ ል ይላሉ:: የአደባባይ ምስጢር የሆኑትን ሌላ ሌላውን ሳንጨምር ይሄ ብቻውን በኦሮሞ ላይ በተለየ የሚደርሰውን ግፍ ባመላከተ ነበር::
ይሄ ጭራ ያስበቀላችሁ የ”ኦሮሞ ፎቢያ” ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ ዋናው አሳሳቢና አንገብጋቢ ጉዳይ አሁን በግብፅ ውስጥ ከለላ የተነፈጋቸው እነዚህ ስደተኞች እስከዛሬ ጥበቃ  እንዴት አያገኙም፤ የወደፊት እጣ ፈንታቸውስ ምንድነው የሚለው ነው:: ችግሩ ያለው ግን ከሞራልና ሎጂክ ውድቀታችሁ ላይ ስለሆነ መነጋገር፣ በቅን መከራከር፣ማስተዋልና መተማመን የሚሉት ባንተና ጌቶችህ ቤት ጨርሶውኑ የሚታሰብ አይደለም::
ለ1 ወር ያክል በተከታታይ ተቃውሞ ሲያሰሙ ማን ዞርብሎ አያቸው? የኢትዮጵያ መንግስትማ ምን ገዶት ያስብላቸዋል:: አይደለም ለ”ዜጎቹ” መብት ሊከራከር እንዲያውም አሁን ከወደቀው የግብፅ መንግስት ጋር በጠረቤዛ ዙሪያ ለመነጋገር የመጀመሪያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ የ”ኦሮሞን ድምፅ አትስሙ” ነው መሰል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የቀድሞው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቢሮ ከሳምንት በላይ ሲደረግና በአገራቸው ሲዘገብ የነበረውን የድረሱልን ጥሪ “አላየንም አልሰማንም” እንዳሉ ተዘግቧል:: በትዊተር ተጠቃሚነታቸው ለሚታወቁት ቴዎድሮስ አድሃኖም እኔም “የአባይ ላይ ጦርነት – እምቢ” የሚለውን ፅሁፌን ጨምሮ በተለይም በኦሮሞ ላይ የሚደረገውን እንዴት ዝም አሉት እያልኩ አጫጭር መልዕክት ስልክ ነበር:: ለነገሩ “እኔና መልዕክቴን ከቁምነገር ይቆጥሩታል፤ ኦሮሞን የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ዜጋ አይቶት ለህልውናው ይቆማል” ብዬ ሳይሆን እሳቸውም “አላየንም አልሰማንም” እንዳይሉ ብዬ ነው:: የህወሃት ምላሽ የትኛውም ቢሆን አያስገርምም፤ የሚደንቀውና የሚያሳዝነው  ከእንዳንተ አይነቱ “ጋዜጠኛ”ና ተቃዋሚ ነኝ ባይ የሚሰነዘረው ውርጅብኝ ነው::  ከ “ብሄር በፊት hhfdሰብዓዊነት” ስትሉ የነበረው ኦሮሞው በግራና ቀኝ ሰብዓዊ መብቱ ሲጨፈለቅ፣ ከመሬቱ ሲፈናቀል፣ በእስር ቤት ሲታጎር፣ሲገደል፣የገባበት ሲጠፋ፣ሲሰደድ፣ልጆቹ ሲደበደቡና ከትምህርት ገበታ ሲባረሩ የት ነበራችሁ፤ የትስ አላችሁ? ድንቄም ሰብአዊነት! ይባስ ብሎ “ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህን ይሻሉ” የሚል ዝግጅት ገና ለገና ይቀርባል ሲባል ዓለምን የሚያስደንቅ የስድብና የጥላቻ ውርጅብኝ! ምንም የማታውቀውን ጋዜጠኛ እስኪያስደነግጥ ድረስ! ዝግጅቱ ከቀረበ በኋላ ያለውን ድራማማ ሼክስፒር ራሱ መድረስ ይከብደዋል:: በተለይ ጃዋርን አብስሎ መብላት ብቻ ነው የቀራችሁ:: እኔን የሚገርመኝ ግን ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ የሞገተውና ገና 30 ዓመት እንኳን ያልሞላው ጃዋር እንዲህ ሱሪ ካስወለቀ ያለማወላወል ኦሮሚያን ነፃ እናወጣለን ብለው ዝንተ ዓመት ሲታገሉ የነበሩት ከእስር ቢፈቱ ወይ ውጭ ያሉት ትግሉን ጠጠር ማረግ ሲጀምሩ ምን ሊኮን ነው? በነገራችን ላይ ይህ የትንሽ ትልቅ ከወደናንተ ሲጠላ ከወደኛ ሲወደድ፣ ከወደናንተ ሲብጠለጠል ከወደኛ ሲወደስ፣ ከወደናንተ ሲናቅ ከወደኛ ሲከበር ላስተዋለና በቅርቡ የኦሮሞ ሳምንትና የአሊ ቢራ በዓል በሚኒሶታ ሲከበር ጃዋርም መሸለሙን ላየ በናንተና በኛ መሃል ያለው ርቀት የትዬለሌ መሆኑን ይገነዘባል::
በተቃራኒው ጎራ ደግሞ ኦሮሞ መሆንህ ኦሮሞን የማጥቃት መብት የሚያሰጥህ ይመስል ዘርህን መቁጠርህ:: አንድም ጊዜ እንኳን ለምንድነው ይሄ ህዝብ እንዲህ የሚሰቃየው፣ ለምንድነው ኦሮሞ በመሆኑ ብቻ የሚታሰረው፣ በአፍሪካ ከሚነገሩ ቋንቋዎች በሶስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ኦሮምኛ ለምንድነው አንድም ነፃ ጋዜጣ የማይታተምበት ያላልክ “ጋዜጠኛ” ዛሬ ዘርህን የምትቆጥር ማንን ለማሞኘት ነው? ስለ እስክንድር ነጋ ሌተ ቀን ስታነበንብ ስለ ሰላሌው ጎበዝ ተማሪ ታዬ ደንደአ(Taayyee Danda’a) መታሰር አንድም ቀን ያልተነፈስክ አስመሳይ ዛሬ ሰላሌን የምትጠራው ማን ይሰማኛል ብለህ ነው? ያንተ ማንነት ነፃነት አያስገኝ፣ ፍትህ አያመጣ፣ ከሰው እኩል አያረግ፣ወይ ከጥቃት አያድን:: ለስም ለስምማ እንኳንስ አንተ በራስህና ለራስህ መናገር እንዲሁም መፃፍ የማትችል ቀርቶ ፈላጭ ቆራጭ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ከኦሮሞና ከጉራጌ ይወለዳሉ:: ግን የሰውዬው የኦሮሞና የጉራጌ ደም ሁለቱን ማህበረሰብ ከብዝበዛ፣ ስድብና የበታችነት ስሜት አላላቀቀ፤ ሰውዬው ራሳቸው ያንን ማንነታቸውን መደበቅ ይፈልጉ እንደነበር ነው የሚነገረው:: እንዲያውም ማንበብና ማወቅ ስለማትፈልግ ወይም ደግሞ እየሰማህ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለህ ነው እንጂ የሰላሌው ምርጥ ልጅና ቀድሞ ንጉሱን ከመፈንቅለ መንግስት በማዳን እንዲሁም ኔልሰን ማንዴላን በማሰልጠን የሚታወቁት ጀነራል ታደሰ ብሩ ከጓዶቻቸው ጋር የኦሮሞ የነፃነት ትግልን የጀመሩት በኃይለስላሴ መንግስት ደረጃ “የኦሮሞን ህዝብ በመቶ ዓመት ወደኋላ ለማስቀረት” የነበረውን ዕቅድ ደርሰውበት ነው:: እናም አልተረዳህ እንደሆነ እንጂ የትኛውም ኦሮሞ ከውጭ ከመጣ ጠላት ይበልጥ የራሱን ከኃዲዎች ይጠየፋል:: ይህን የምለው ወይ አንተን ለማስተካከል አሊያም ኦሮሞውን ወጣት ገልቱ ታረጋለህ ብዬ ሰግቼ ሳይሆን ኦሮሞ ያልሆነውን ሌላውን ህብረተሰብ ያለትክክለኛ መረጃ እያወናበድክ በኋላ አለመግባባት እንዳይፈጠር ነው::
በተረፈ የዘፋኙን መልዕክት ስለመረዳትህ እርግጠኛ ባልሆንም ስለጋበዝከን ዘፈን አመሰግናለሁ:: እኔ ደግሞ ይህን ግጥም ልጋብዝህ
” . . .Ni aara naan jedhu obsee hin dabarfatu
Madaa koo kanatti falaxaa itti horfu
Isan an sossobee kunuunse kunuunsee  qoorsu
Isaan guyyaa guyyaan na jalaa boochisu
Miirri dhukkubbii isaa qaama koo bobeessaa
Muddaa mudhiin isaa na dhoweera deemsa
Madaa kootu hin qooru maafan aaruu dhiisa”
ሙሉውን ግጥም (በግርድፍ ትርጉም “ቁስሌ አልደረቀም ለምን አልናደድ” ፀኃፊ ተስፋዬ ብርመጂ) ከጉለሌ ፖስት ማግኘት ትችላለህ:: አሁንም እንደቀድሞው “ማንብብ ሳይጠበቅብኝ አውቀዋለሁ” ብለህ እንደማትዘለው ተስፋ አደርጋለሁ:: ቁቤ አላውቅም ኦሮምኛ አላነብም የሚል የሰነፍ ሰበብ ታመጣለህ ብዬ አልጠብቅም:: “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” አይደል የሚባለው? ፍንፊኔ/አዲስ አበባ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ በሁለት ወር የጨረስኩትን አንተ በዚህ እድሜና እውቀት ይከብደሃል ካሉኝ አላምንም::  ምናልባት ኦሮምኛ መማርህ አማርኛን ያስጠፋብኛል ብለህ ሰግተህ ከሆነ በኔ ይሁንብህ፤ አንዳንድ ዘለፋዎችን ያስረሳህ ይሆናል እንጂ ቋንቋው በጭራሽ አይጠፋብህም::
በመጨረሻም አያቶቼ በኦሮምኛ የመከሩኝን ትንሽ ምክር ተርጉሜ ላካፍልህ:: “አንገትህን ቀና አድርገህ ሂድ: ማንነትህ ከማንም ቡራኬ(ወይም ግሳፄ) ሳያሻው ላንተ በቂ ነው:: ራስህን ከመጠን በላይ አትውደድ፤ ነገር ግን እራስህንና እኛን ከሚያስጠላህና የበታች ከሚያረግህ ነገር ራቅ፤ እኛና የወለድናቸው ወላጆችህ እንደምንወድህ አንተ ደግሞ አክብረን፤ ወንድሞችህን ውደድ፤ ለልጆችህም ይህን አስተምር:: ” ምናልባትም አያቶችህና በፅሁፍህ የጠቀስካቸው በኦሮሚያ ውስጥ ስትዘዋወር ያገኘሃቸው አዛውንቶች ተመሳሳይ ምክር ሊመክሩህ ይችሉ ነበር፤ ነገር ግን ቋንቋቸውን አታውቅምና የሚሉትን ስላማትረዳ የሰጡህን እርጎ ብቻ ጠጥተህ ሄድክ:: በወንድሞችህና በልጆቻቸው ላይ ያለምንም ርህራሄ(ምናልባትም በግፊት)  የፃፍከውን አሁን ቢያውቁ እንዴት ይፀፅታቸው ይሆን? ሰላሌ ጉድ ካለ ልጆቼ ለምን ጥበቃ ጠየቁ ብሎ ሳይሆን ያንተና መሰሎችህን እርቢተኝነት አይተው ወንድም በወንድሙ ላይ ሲነሳና በዙሪያው ያለው ሁሉ ዝም ሲል(አንዳንዱም ድንጋይ ሲያቀብል) ታዝበው ነው:: ኦሮሞውንም ሆነ ሰብዓዊነት የሚሰማውን የትኛውንም ማህበረሰብ ጉድ የሚያሰኙት ካገራቸው በግፍ መሰደዳቸው ሳያንስ በስደት በሚኖሩበት በማያውቁት ነገር ሲጠቁ መግቢያ ጠፍቷቸው ከለላ የጠየቁት  ሳይሆኑ በአደባባይ እነሱን ስትዘልፉ ውላችሁ ሰው አይሰማንም በማለት ከጓዳችሁ የምትሰሩት ስራ የተጋለጠባችሁ ናችሁ:: ኤልያስ ክፍሌ ከሞቀ ጎጆው ለግብፅ የተማፅኖ ደብዳቤ ሲፅፍ አቀርቅራችሁ አሳልፋችሁ ስደተኞች መፈክር አነገቡ ብላችሁ የምትንጫጩት ናችሁ ጉደኞች:: ትምክህት፣ ጥላቻና ስድባችሁ ዓለምን ጉድ ያሰኘው ናችሁ የታሪክ ጉደኞች::
የግርጌ ማስታወሻ
በደመ ነፍስ ለፃፍከውና በመረጃ ዕጦት/መዛባት ዕርቃኑን ለቀረው የመጀመሪያው ፅሁፍህ የነበረው አድናቂ ብዛት በተለይም ደግሞ ለዘብ ካለውና ስህተትህን ሙሉ በሙሉም ባይሆን በከፊሉ አምነህ ይቅርታ ከጠየቅክበት ፅሁፍህ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አሳሳቢ ነው(2000+ ለ 500 የፌስቡክ አዎንታዊ ምላሽ)::  አንተና ቀጣሪዎችህ የአንባቢያችንና የአድናቂያችን ብዛት የአስተሳሰባችን ትክክለኛነ ት መገለጫ ነው ካላችሁ እኔ ደግሞ የምታራምዱት የብሄር ጥላቻ ፕሮፓጋንዳ መረን የመልቀቁ ውጤት ነው እላለሁ:: ትግሬውንስ ስልጣን ቀማን ብላችሁ ነው እንበል፤ ኦሮሞውስ ምን አድርጎአችሁ ነው? ይህን ትልቅ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከተረባረባችሁበት ሌላው በቁጥር ያልበዛውማ ትምሩኛላችሁ ብሎ የሚያምን ይመስላችኋል? እናንተ ምናልባት ከግራ የቆሙትን ጎትተን ወደ ቀኝ እናመጣቸዋለን ብላችሁ ከሆነ እኔ ደግሞ ሲጀመር የምትጎትቱት ጠንካራ ገመድ ሳይሆን ቀጭን ክር ነው፤ ሲቀጥል ደግሞ የምትጎትቱት እናንተ ብቻ አይደላችሁምና ያቺ ክር ልትበጠስ እየተቃረበች ነች ባይ ነኝ:: የሚያሳስበኝ የክሩ መሳሳት ሳይሆን የዚህ የብሄር ጥላቻ ዘመቻ መዘዝ ነው:: የዛሬዋ ኢትዮጵያ የወደ ፊት ዕጣ ፈንታ የትኛውንም ይሁን በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ህዝቦችና ብሄሮች ያሉበት ቦታ እንዳሉ መቆየታቸው የግድ ነው:: በሰሜን አማራና ደቡብ ትግራይ፣ ሰሜን ኦሮሚያና ደቡብ አማራ፣ ምስራቅ ኦሮሚያና ኦጋዴን ወዘተ የሚኖሩ ህዝቦችና ብሄሮች ጎረቤት ሆነው ይቀጥላሉ:: በተለያዩ የደቡብ ከተሞች ውስጥ የተለያዩ ብሄረሰቦች በተለይም አማራው ከረጅም ጊዜ አንስቶ እንደሚኖሩት ወደፊትም ይኖራሉ:: እናም የትኛውንም የፖለቲካ አቅጣጫ የሚከተል ለነዚህ ዜጎች የወደፊት ሰላም ቅድሚያ ካልሰጠ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው አህያ የሚያስብ መሆን አለበት::  ዛሬ በተገኘው አጋጣሚና በየሚድያው የጥላቻ መርዝ እየተዘራ ነገ የሰላም ፍሬ መጠበቅ ወይ ከሞኝነት የመነጨ ነው አሊያም አጉል ግትርነት ነው::  ዛሬ በህወኃት መንግስት የተቆጣጠረው ሚዲያ ቀስ በቀስ ወደ አንጀት ቁስልነት ተሸጋግሮ ባለበት ሰዓት በአንዳንድ ድርጅቶች ቁጥጥር ስር ያሉት ሚዲያዎች ገና ስልጣን ሳይኖራቸው የጨጓራ በሽታ ከሆኑ ስልጣን ቢያገኙማ ወዴት እንደሚሸጋገሩ መገመት አያዳግትም::

ቸር እንሰንብት::
ግርማ ታደሰ
ሃምሌ 9 2013

No comments:

Post a Comment