Pages

Tuesday, February 10, 2015

ከዚህ በላይ ዉርደት የለም – የወያኔ ሴራ ከነፃነት ትግሉ አያግደንም!


ከከልለው ኡርጋ*
ከዚህ በላይ ዉርደት የለም
ሁሉም የእግዚሀብሔር ፍጥረቶች – ሰዉ እና እንሰሳት ጭምሮ – ምንም እንኳን ዓይነት እና ደረጃዉ የተለያየ ቢሆንም፣ መብት አላቸው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ አደጉ እና ሰለጠኑ የምንላቸው የዓለማችን ሀገሮች፣ የእንሰሳት መብት ከሰው ልጅ መብት ባልተናነሰ ሁኔታ የሚከበርበት ደረጃ ላይ ተደርሶል። የነሱን መብት መጠበቅም ልክ እንደ አንድ የእድገት ደረጃ መቆጠር ከጀመረ ውሎ አድሮል። እነሱም ልክ እንደ አንደ ሰው ፍላጎት እና ስሜት አሏቸው ለምሳሌ ያህልም:- የህመም፣ የደስታ፣ የፍራቻ፣ የብቸኝነት፣ የስቃይ እና የእናት ፍቅር የመሳሰሉት ናችው። ለዚህም ነው ፍላጎታቸውን እና ስሜታቸውን የሚቃረን ተግባር መፈፀም የለበትም፣ የሚሉ አያሌ የእንሰሳት መብት ተሞጋቾች የሚቃወሙት እና የሚታገሉት። መሀተመ ጋንዲ በአንድ ወቅት “የአንድ ሕዝብ ታላቅነት የሚለካው ወይም የሚመዘነው ወይም የሚዳኝው፣ ለእንሰሳት በሚሰጡት እንክብካቤ ነው ያሉት።”
ዛሬ ግን፣ ምስኪኑንና ለፍቶ-አደር የኦሮሞ ገበሬና ለነፃነት፣ ለእኩልነት እና ለፍትህ ብሎ የሚታገለውን እና ለአምባገነኑ የወያኔ መንግስት አልገዛም ያለውን ኦሮሞ፣ ሰባዊ ከሆነ የፍጡር ደረጃ አወረዱት። ዛሬ ዓለም ለእንሰሳት ከምትሰጠው ክብር በታች አውርደውት፣ ልክ እንዳልባሌ ቁስ/ነገር ቆጠሩት። ሰውን የሚያክል ክቡር ፍጡርን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደሉ በኃላ፣ መሬት ለመሬት እየጎተቱ በአደባባይ መስቀላቸው፣ ያቺ ሀገር መንግስት-አልባና በተደራጁ የሽፍቶች ቡድን የምትገዛ መሆኖን ማሳያ ነው።
Oromo in Salale Murdered Dragged and Displayed 2015 2
እነሱ ብቻ በተቆጣጠሩት የመገናኛ ብዙሀን፣ የራሳቸውን የሽፍታነት ተግባር፣ ለነጻነት ታጋዩ ምስኪን ገበሬ ይለጥፉለታል። “አሽባሪ፣” “ጠባብ፣” “ሽፍታ፣” “ገንጣይ፣” “አስገንጣይ፣” “ጎጠኛ” ወዘተ … ይሉታል። ደርግም አኮ ‘ፀረ-ህዝብ፣’ ‘ፀረ-አብዮት’ አያለ ነበር እኮ፣ ሕዝብ ሲፈጅ የነበረው። እነዚህም በተመሳሳዩ፣ የተለያየ ታርጋ እየለጠፉ ሕዝቡን ጨረሱት። ታድያ እንዴት አንድ ጭብጥ ነቀዝ ወያኔን ማስወገድ አቅቶን፣ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ የተሞላበት ኢ-ሰባዊ የሆነ ድርጊት እና የሥም ማጥፋት ዘመቻ በሕዝባችን ላይ እስከ-መቼ ሲፈፅመ ይኖራሉ? ነቀዝያልኩት ለመሳደብ ፈልጌም አይደለም፣ ስድብ የኦሮሞ ባህልም አይደለምና። ቃሉን የተጠቀምኩት የወያኔን እና የነቀዝን ተመሳሳይነት እና አንድነት ለማሳየት ነው። ሁለቱም ውስጥ ውስጡን እየበሉ ባዶ የሚያስቀሩ ተዋስያን ስለሆኑ ነው። በመሀከላችን የገቡትን እነዚን ተዋሲያን፣ በመረባረብ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ማስወገድ ካልቻልን፣ በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አናመልጥም – ሌላም አካል ሊያስወግድልን አይመጣም። “Surre jilbaa irraan dhumtee abbaatu warranata degaa ijjollummaan dhuftee abbaatu tattafata” ይባላል።
ተማሪውን፣ ገበሬውን፣ ሰራተኛውን – ከሕፃን እስከ አዋቂ – ገደሉ፣ አሰሩ፣ አፈናቀሉ፣ አሰደዱ፤ የምንመካበትን የተፈጥሮ ሀብት መዘበሩ፣ ትላልቅ መሬቶቻችን ወሰዱ፣ ወንዞቻችንን መረዙ። ከዚህም አልፈዉ፣ የምስኪኑን ገብሬ ሬሣ በራሱ ቄዬ ላይ፣ በወገኖቹ ፊት፣ መሬት ለመሬት ጎተቱ፣ እጅ እና እግሩን ጠፍንገዉ ሰቀሉ – ከዚህ በላይ ለኦሮሞ ሕዝብ ሞት ምን አለ? ከዚህ በላይ፣ ወርደት ከወዴት ይመጣል?
የወያኔ ሴራ ከነፃነት ትግሉ አያግደንም!
የኦሮሞ ሕዝብ በዚያች ሀገር ላይ በብዛት ግንባር ቀደም ነው። የኦሮሞ ሕዝብ፣ ከሌሎች ከተጨቆኑ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር በመሆን፣ በዚያች ሀገር ላይ ነፃነት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ሊጭወት ይችላል። ሕዝብ ደግሞ በየትኛውም ዘርፍ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት አካል ነው። ያለ ሕዝብ ተሳትፎ ሁለንተናዊ እድገት እና ነፃነት የማይታሰብ ነው። በተለያየ ግዜም ሕዝብ፣ አምባገነን መንግስት-ተብየው አካል ጋር እንዳሆነ አሳይቶል፤ ወያኔም፣ ሕዝብ አልባ አንደሆነ ይታወቃል። እየደረሰብን ካለው ውርደት ለመዉጣት አና ነፃነታችን ለመጎናፀፍ፣ እያንዳንዳችን ባለን አቅም እና ችሎታ የምናበረክተው አስተዋፆ፣ ለትግሉ አንድ ደረጃ መድረስና ለነፃነታችን እውን መሆን ወሳኝነት አለው። ይህ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ድርጊት የመታገል፣ የሁላችንም ግዴታ ነዉ።
ድል ለኦሮሞ ሕዝብ!
ከልለው ኡርጋ:- kiyu297@gmail.com