ሞትን የናቀና እስራትን ያልፈራ ትውልድ ተራራዉን ይንዳል!

barruu

“የቆጡን ላውርድ ብላ የብብቷን ጣለች::” ይላሉ ዐበው ሲተርቱ። ይህች ምስኪን ስግብግብ ፍጡር ሌላውን ስታሳድድ የያዘችው ሁሉ ይበተንባታል:: ሰሞኑ በሀበሾቹ መንደር ስጋቱ አይሏል፤ ግርግሩም በርትቷል:: እንደ ማባበልም፣ እንደ ማስጠንቀቅም፣ እንደ መቆጣትም፥ ብቻ ነገሩን በያይነቱ እየሞካከሩት ነው። እንዳለመታደል ሆኖ ለዚህ ሁሉ ችግራቸውና ስጋታቸው ምንጩ የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ትግል እንደሆነ ሊያስረዱን ይሞክራሉ። በመሠረቱ የኦሮሞ ህዝብ ትግል ዓላማና ግቡ ጨቋኝ ቅኝ ገዥዎችን ማስወገድና በአንጻሩ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ የሚካሄድ ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች መሠረት ያለው ፍትኃዊ ትግል ነው። የዚህ ትግል ጠቀሜታ ለኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የቅኝ ገዥዎች ቀንበር በኃይል ለተጫነባቸው ለመላው የኢምፓየሪቷ ብሔሮችና ህዝቦች ጭምር ነው። በመሆኑም የኦሮሞ ሕዝብ በጭቁን ሕዝቦች የጋራ ትግል ያምናል። መሰል ዓላማና ግብ ካላቸው ኃይሎች ጋር የተቀናጀ የጋራ ትግል ያካሄዳል፤ በማካሄድ ላይም ነው። በሌላ መልኩ የኦሮሞ ህዝብ በሁለንተናዊ ባሕሪውም ሆነ በባሕላዊ አደረጃጀቱና አስተዳዳራዊ መዋቅሩ ሠላምን ይሰብካል፤ ፍትሓዊ አንድነትን ያበረታታል። ደካማውን ያፀናል፤ የተገፋውን ያቋቁማል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በዛሬዋ ኦሮሚያ ውስጥ ለዘመናት የኖሩ ብሔሮችና ሕዝቦች በፀረ-ኦሮሞ ኃይሎች የሚደረገውን እኩይ የማጋጨት ሤራ በማክሸፍ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ያላቸውን ተምሳሌታዊ አንድነት እንዴት ጠብቀው እንዳቆዩ ልብ ማለት ያሻል።
በአጠቃላይ የኦሮሞ ሕዝብ በማሕበራዊ አኗኗርም ሆነ በብሔራዊ ትግሉ የሰብኣዊ መብቶችን ቀመር በወጉ የተከተለ በመሆኑ በማንኛውም መመዘኛ ለጎረቤት ሕዝቦችም ሆነ አብረውት ለሚኖሩ ወንድም ሕዝቦች ስጋት ባለመሆኑ የነፍጠኛ ሥርዓት ናፋቂ ኃይሎችና አብዮታዊ ህወሃቶች(TPLF) የኦሮሞ ሕዝብን በአጠቃላይ፥ ብሔራዊ ትግሉን ደግሞ በተለይ ለማጥላላት በጋራና በተናጠል የሚያራግቡትን መሰረተ-ቢስ ወሬና የሚያደርጉትን ከንቱ ሙከራ በቀላሉ ፉርሽ ያደርጋል።
ይህ  እውነታ በተለያዩ ጊዜ በተለያዩ ሰዎች ሲገለፅ ቆይቷል።  ሆኖም ግን  ይህንን መረዳት የተሳናቸው ኦሮሞ-ፎቢክ የሆኑ (Oromo-phobia) ፍርሃተ-ኦሮሞየተጠናወታቸዉ ኃይሎች ተገደውም ብሆን እጃቸውን እስኪሰጡ ድረስ የኦሮሞ ትግል እምርታ በቃልም ሆነ በተግባር ልናሳያቸውና ልናስተምራቸው ግድ ይለናል። በዚሁ መሠረት የኦሮሞ ህዝብ ትግል በማንኛውም ዓይነት ሤራ መቀልበስ የማይቻል እጅግ ወሳኝ ደራጃ ላይ ስለመድረሱ ባይወዱም ምስጢን ከነተጨባጭ መስረጃዎቹ  ላሳያችሁ ወደድኩ።
ማሳያ ቁጥር አንድ፥ የኦሮሞ ሕዝብ ውድ ልጆቹ በከፈሉት ክቡር ዋጋ የሀገሩን ድንበርና የህዝቡን እውነተኛ ታርክ እስከ ወዲያኛው የዓለም ጫፍ ድረስ ለማስተዋዋቅ ችሏል። ከእንግዲህ ወዲያ ሀገራችን ኦሮሚያ በልጆቿ ደምና አጥንት እስከ ዘልዓለሙ ትከበራለች!!። በቃ እውነታው ይህ ነው።